የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ እንዳሻው ጣሰው በክልሉ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሁራን ጋር እየመከሩ ነው

By Tamrat Bishaw

May 20, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው በክልሉ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሁራን ጋር በሆሳዕና ከተማ እየመከሩ ነው።

በውይይት መድረኩ የዋቻሞ፣ የወልቂጤና የወራቤ ዩኒቨርሲቲዎች አመራሮችና ምሁራን እየተሳተፉ ሲሆን፤ ተቋማቱ በክልሉ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ባህላዊ፣ የቴክኖሎጂና ሌሎችም መስኮች ፈጣን ለዉጥ ለማምጣት የሚያግዝ ጉልህ አስተዋጽኦ በሚያበረክቱባቸዉ መስኮች ዙሪያ የሚመክር መሆኑ ተመላክቷል።

መድረኩ የጋራ አረዳድ፣ ዝግጁነት፣ ተቀራራቢ የዓላማና የተግባር ዉህደት በመፍጠር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የክልሉን ሁለንተናዊ ልማት ለማፋጠን አጋዥ እንደሚሆኑ መገለጹን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በመድረኩ የክልሉ መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲዎቹ ፕሬዚዳንቶችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።