አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንግሥት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያከናውነውን የአረንጓዴ ልማት ሥራ ለመደገፍ የጀመረችውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል ኖርዌይ አስታወቀች።
ኖርዌይ የኢትዮጵያ መንግሥት በአየር ንብረትና በብዝኃ-ሕይወት ጥበቃ ላይ የያዘውን ግብ ለመደገፍ ኖርዌይ እየሠራች መሆኗን በኢትዮጵያ የሀገሪቱ ኤምባሲ የአየር ንብረት፣ አካባቢና ደን አማካሪ ማሪ ማርቲንሰን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በብዝኃ-ሕይወት ጥበቃ ላይ በርካታ ተግባራትን እያከናወነች መሆኗን ጠቅሰው÷ በተለይም በደን ጥበቃ ላይ እየተሠራ ያለው ሥራ አበረታች መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያከናውነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብርም ለአረንጓዴ ልማት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ለብዝኃ-ሕይወትና ለመጪው ትውልድ ስጋት በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸው÷ ሌሎች አጋር አካላትም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኖርዌይ የአየር ንብረትና አካባቢ ሚኒስትር የካቲት 2016 ዓ.ም ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በአየር ንብረት ላይ ያለውን አጋርነት እስከ ፈረንጆቹ 2030 ለማጠናከር መስማማቱንም አስታውሰዋል፡፡
በዓለም ላይ ብዝኃ-ሕይወትን ጠብቀው በማቆየት ስኬታማ ከሆኑ 36 አካባቢዎች ሁለቱ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኙ አመላከተው ሀገራቸው ለእነዚህ አካባቢዎች ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል፡፡