አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ጠንካራ ተሳትፎ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝግጅቶችን እያደረገች መሆኗን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ከአኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ጋር በተገናኘ የጉሙሩክ እንቅስቃሴን ለማሳለጥ ዘመናዊ አሠራር እየተዘረጋ መሆኑን በኮሚሽኑ የታሪፍና ስሪት አገር ዳይሬክተር ካሳዬ አየለ ገልጸዋል፡፡
ለአብነትም የድንበር አሥተዳደርና የካርጎ ፍተሻን ኤሌክትሮኒክ ማድረግን ጨምሮ በድሮን የታገዘ የክትትል ሥርዓት መዘርጋቱን ጠቅሰዋል፡፡
በነጻ የንግድ ቀጣናው የዚህ አሠራር ተግባራዊ መሆን ደግሞ በዕቃዎች መተላለፍና ግብይት ወቅት በቀላሉ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ የሚያስችል መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
በነጻ ንግድ ቀጣናው የሚነግዱ አባል ሀገራት የሚያቀርቡት ምርት በራሳቸው የተመረተ መሆን ስላለበት በነጻ የንግድ ቀጣና የስሪት ሀገር ሕግ መሰረት የተመረተ መሆኑን ማረጋገጫ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋ፡፡
የአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና በመላው አፍሪካ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን÷ 3 ነጥብ 4 ትሪሊየን ዶላር ዓመታዊ ምርት ድርሻ እንደሚኖረው ይገመታል።