የሀገር ውስጥ ዜና

በጤናው ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት ተመዝግቧል – አቶ አሻድሊ ሃሰን

By ዮሐንስ ደርበው

May 19, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጤናማ እና አምራች ማኅበረሰብ ለመፍጠር በተከናወኑ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ውጤት መመዝገቡን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሃሰን ገለጹ፡፡

አቶ አሻድሊ በአሶሳ ዞን መንጌ ወረዳ ከ40 ሚሊየን ብር በሚልቅ ወጪ ለሚገነባው የካሻፍ ቱመት መንገዱል ጤና ጣቢያ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡

በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግርም÷ ባለፉት ዓመታት በክልሉ በጤናው ዘርፍ ጤናማ እና አምራች ማኅበረሰብ ለመፍጠር በተከናወኑ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል፡፡

ዛሬ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት ጤና ጣቢያ በአዲሱ የጤና ፖሊሲ ደረጃ እንደሚገነባ ማስታወቃቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡

የሚገነባው የጤና ጣቢያ ወጪ በክልሉ ቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት እንደሚሸፈን እና ግንባታውም ከ6ወር እስከ አንድ ዓመት እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል፡፡

ግንባታው ሲጠናቀቅም ከ30 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች አገልግሎት እንደሚሰጥ ተመላክቷል፡፡