ስፓርት

በፕሪሚየር ሊጉ ቫር ተግባራዊ እንዳይደረግ የሚያስችል ድምጽ ሊሰጥ ነው

By Mikias Ayele

May 16, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች በሚቀጥለው የውድድር ዓመት በተንቀሳቃሽ ምስል የታገዘ ዳኝነት (ቫር) ተግባራዊ እንዳይደረግ የሚያስችል ድምጽ ሊሰጡ መሆኑን ፕሪሚየር ሊጉ አስታውቋል፡፡

ቫር በፕሪሚየር ሊጉ ከፈረንጆቹ 2019 ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን÷የተወሰኑ ክለቦች በቫር ውሳኔ ደስተኛ አለመሆናቸውን እና እግር ኳሱን እየረበሸው እንደሚገኝ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡

በቫር ቅሬታ ካለባቸው ክለቦች አንዱ የሆነው ወልቨርሃምፕተን ቫር ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ እንዳይደረግ የሚያስችል ውሳኔ ሃሳብ ያቀረበ ሲሆን÷ፕሪሚርሊጉም ምላሽ ሰጥቷል፡፡

በምላሹም በፈረንጆቹ የፊታችን ሰኔ 6 ቀን በሚደረገው የክለቦች ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ በጉዳዩ ላይ ድምጽ እንደሚሰጥ ነው ያስታወቀው፡፡

ወልቭስ ባቀረበው ቅሬታ መሰረት በፕሪሚየር ሊጉ ከሚገኙ 20 ክለቦች 14ቱ ቫር እንዲታገድ ድምጽ የሚሰጡ ከሆነ ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ቫር በፕሪሚር ሊጉ ተግባራዊ ላይሆን እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡

ቫር ቀደም ሲል ግብ ከተቆጠረ በኋላ በንክኪዎች እና ከጨዋታ ውጪ በሆኑ ምክንያቶች ግቦች እንዳይጸድቁ ማድረጉ ደጋፊዎችን እያበሳጨ ነው በሚል ቅሬታ ሲቀርብበት ቆይቷል፡፡

በተጨማሪም ቫር ጨዋታዎችን ለመፈተሽ የሚወስደው ጊዜ እና የቫር ዳኞች የሚፈጽሟቸው የእይታ ስህተቶች የእግር ኳስ ቤተሰቡ ቫር ላይ ያለውን እምነት እያሳጣው እንደሚገኝ መገለጹን ሲኤን ኤን ስፖርት ዘግቧል፡፡