አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 90 በመቶ የሚሆነው የሩሲያና ቻይና ግብይት በሀገራቱ መገበያያ ገንዘብ የተፈጸመ መሆኑን የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ገለፁ፡፡
ፕሬዚዳንት ፑቲን ለሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ትናንት ቤጂንግ የገቡ ሲሆን ከቻይናው አቻቸው ዢ ጂንፒንግ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸው በሞስኮ እና በቤጂንግ መካከል ያለው ግንኙነት በጋራ መከባበር፣ በመልካም ጉርብትና እና በጋራ ጥቅም መርህ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ፕሬዚዳንት ፑቲን ተናግረዋል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እና የሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት በሁለቱ ሀያላን ሀገራት እድገት ላይ ተፅዕኖ ቢያሳድርም ሀገራቱ ጠንካራ የኢንቨስትመንት ትብብር በመገንባት የንግድ ልውውጣቸውን እያሳደጉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በተለይም 90 በመቶ የሚሆነው የንግድ ልውውጣቸውን በሩብል እና በዩዋን እንዲገበያዩ የተደረገው ውሳኔ በመካከላቸው ጠንካራ የንግድ ትስስር መሰረት መጣሉን ጠቁመዋል።
የሀገራቱ የንግድ ልውውጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 227 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ ተገልጿል።
ፕሬዚዳንት ፑቲን በቤጂንግ በሚኖራቸው ቆይታ በሀገራቱ በሁለትዮሽ ግንኙነት፣ በኢኮኖሚ ትብብር፣ በዩክሬን ግጭትን እና በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አር ቲ ዘግቧል፡፡