የሀገር ውስጥ ዜና

8ኛው አመታዊ የምርምር አውደጥናት እየተካሄደ ነው

By Amele Demsew

May 16, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ 8ኛውን አመታዊ የምርምር አውደጥናት እያካሄደ ነው፡፡

“ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራ” ለኢንዱስትሪ በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው አውደጥናቱ በዋናነት ለኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ ግብዓት ይሆናል ተብሏል።

አውደጥናቱን በይፋ ያስጀመሩት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) ÷ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሀገር ግንባታና የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማሳደግ ሚናቸው ከፍተኛ በመሆኑ በሚያደረጉት የምርምር ስራ ብዙ ይጠበቃል ብለዋል።

የምርምር አውደጥናቱ ለፈጠራ እንደእርሾ ሆኖ ያገለግላል ያሉት የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ደረጄ እንግዳ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎችም ከፍተኛ አበርክቶ እንደሚኖረውም ነው የገለፁት፡፡

እንዲሁም ለተመራማሪዎችና ለምሁራንም ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በአውደጥናቱ ላይ የተለያዩ ጥናትና ምርምሮች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ሲሆን÷ መድረኩ ዛሬና ነገ እንደሚካሄድ ነው የተጠቆመው።

በዓለምሰገድ አሳዬ