አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ የማጥቃት ዘመቻ መበርታቱን ተከትሎ ዩክሬን ወታደሮቿን ከካርኪቭ ግዛት ድንበር አካባቢ ከሚገኙ በርካታ መንደሮች እንዲያፈገፍጉ ማድረጓ ተገለጸ፡፡
የዩክሬን ጦር ቃል አቀባይ እንደተናገሩት፤ ወታደሮቹ በከባድ ተኩስ ውስጥ አልፈው ወደ ሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል ይበልጥ ምቹ ወደ ሆኑ ሁለት አካባቢዎች ተዛውረዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪም ወታደሮቻቸው አዲሱን ድንበር ተሻጋሪ ያሉትን ወረራ ለመቆጣጣር እየታገሉ መሆናቸውን ተከትሎ ሁሉንም የውጭ ጉዞዎች መሰረዛቸው ተገልጿል።
የፕሬስ ፀሐፊያቸው ሰርጊ ኒኪፎሮቭ፤ ፕሬዚዳንቱ በሚቀጥሉት ቀናት ለማከናወን ያቀዷቸው ሁሉም ዓለም አቀፍ ዝግጅቶች እንዲራዘሙ እና ለሌላ ጊዜ እንዲሸጋገሩ መመሪያ መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
የሩሲያ ጦር ኃይል በአሁኑ ጊዜ በአካባቢው ሁለት ተጨማሪ መንደሮችን÷ ሉኪያንትስኪ እና ሂሊቦኬ እንዲሁም በደቡብ ዛፖሪዢያ ግዛት የምትገኘውን የሮቦቲን መንደር መቆጣጠሩን ገልፃለች።
ይሁን እንጂ በእዚህ ጉዳይ ላይ ከዩክሬን በኩል እስካሁን የተሰጠ አስተያየት አለመኖሩን ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል፡፡