Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በብልጽግና ፓርቲ እና ሕወሓት መካከል የተጀመረው የፓርቲ ለፓርቲ ፖለቲካዊ ውይይት በመቀሌ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በብልጽግና ፓርቲ እና በሕወሓት መካከል የተጀመረው የፓርቲ ለፓርቲ ፖለቲካዊ ውይይት ለሦስተኛ ጊዜ በመቀሌ ከተማ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል::

በውይይቱም÷ ቀደም ሲል የተደረሰውን የፓርቲ ለፓርቲ የግንኙነት መርሆዎች በማስታወስና የተጀመሩትን ዋና ዋና አጀንዳዎች የመለየት ሂደት በማጠናቀቅ በአጀንዳዎቹ ቅደም ተከተል ላይ መክረዋል፡፡

ከምክክሩ በኋላም የጋራ መግባባት ላይ መደረሱ ነው የተገለጸው፡፡

በመጀመሪያ አጀንዳነት የተለየውን ከዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ ጋር ተያይዞ በዝርዝር ውይይት በማድረግ ሁለቱም ፓርቲዎች ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ በጋራ በቁርጠኝነት ለመስራት ተስማምተዋል፡፡

እንዲሁም፡-

1. በቅርቡ በራያ የተፈጠረውን የግጭት ክስተት በተመለከተ በዝርዝር ውይይት በማካሄድ፣ ክስተቱ መፈጠር ያልነበረበትና ከጀመርነው ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ ሂደት ጋር የሚቃረን እንደሆነ መግባባት ላይ ደርሰዋል::

2. ማንኛውንም ጉዳይ በሰላማዊ መንገድና በውይይት እየፈቱ ለመሄድ ሁለቱም አካላት የበኩላቸውን ፓለቲካዊ ድርሻ ለመወጣትና በቁርጠኝነት ለመስራት ተስማምተዋል::

በተያያዘም የሚኖሩ የኮሙኒኬሽን ስራዎች የሰላም ሂደቱን የሚደግፉ እና ግጭት ቀስቃሽ ከሆኑ ንግግሮችና ይዘቶች የተቆጠቡ እንዲሆኑ መግባባት ላይ ደርሰዋል ::

3. ማናቸውንም ግጭት የሚፈጥሩ አዝማሚያዎችን በጋራ ለመከላከል እና ከተፈጠሩም በፍጥነት ለመቆጣጠር በቁርጠኝነት ለመስራት ተስማምተዋል::

4. የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ወደ መሬት ለማውረድ እየተሰሩ ላሉ ስራዎች ስኬት ምቹ ፖለቲካዊ ሁኔታ ለመፍጠር ሁለቱም ፓርቲዎች ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

በቀጣይም በሌሎች አጀንዳዎች ላይ ለመወያየት በመስማማት የዕለቱን ምክክር አጠናቅቀዋል፡፡

Exit mobile version