የሀገር ውስጥ ዜና

በኢትዮጵያ የምግብ ስርዓትና ስነ-ምግብ ፍኖተ ካርታ ላይ ምክክር ተካሄደ

By Tamrat Bishaw

May 14, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንግስት እና የልማት አጋሮች ቡድን በሀገሪቱ የምግብ ስርዓት እና ስነ-ምግብ ፍኖተ ካርታ ላይ የምክክር መድረክ አካሂደዋል።

በግብርና ሚኒስቴር እና በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እየተመራ ያለው ፍኖተ ካርታ ሀገሪቱ አሁን ያለችበትን የምግብ አሰራርና ስነ-ምግብ ሂደት ለመለወጥ ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ይህም በሰባት ክላስተሮች የተደራጁ 24 የመፍትሄ ሀሳቦችን የለየ ሲሆን፤ በስድስት ወሳኝ አጋሮች እየተደገፈ መሆኑ ተመላክቷል።

ለሀገር አቀፍ ባለድርሻ አካላት ተግባራዊ መመሪያ ሆኖ ያገለግላል የተባለለት ፍኖተ ካርታ፥ ጥረቶችን ወደ አንድ የጋራ የምግብ ስርዓት ራዕይ እና የስነ-ምግብ ለውጥ ለማምጣት ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል።

የልማት አጋሮች በቴክኒክና በገንዘብ የሚያደርጉትን ድጋፍ ከፍ ለማድረግ ቃል የገቡ ሲሆን፤ ይህንን የለውጥ ተነሳሽነት ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነትም ገልጸዋል።

መንግስት የልማት አጋሮችን በሁሉም የምግብ ስርዓት እና ስነ ምግብ ፍኖተ ካርታ ለማሳተፍ ያለውን ቁርጠኝነትና የቀረቡ አስተያየቶችንም ከግምት እንደሚያስገባ ማረጋገጡን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።