Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በሣይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ ላይ ያተኮረ ኤክስፖ ሊዘጋጅ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) “ስትራይድ ኢትዮጵያ 2024” የተሰኘ ትኩረቱን በሣይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ ላይ ያደረገ ኤክስፖ በአዲስ አበባ ሣይንስ ሙዝየም ሊካሄድ ነው።

ኤክስፖው “ሣይንስ በር ይከፍታል፤ ቴክኖሎጂ ያሥተሣሥራል፤ ፈጠራ ወደፊት ያራምዳል” በሚል መሪ ሐሳብ ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ እንደሚከፈት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴዔታ ይሽሩን ዓለማየሁ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

እንዲሁም ከግንቦት 11 እስከ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ሣይንስ ሙዝየም ለሕዝብ ክፍት እንደሚደረግ አመላክተዋል፡፡

በኤክስፖው ከ30 በላይ የመንግሥት ተቋማት፣ ከ40 በላይ ባንኮች እና ኢኮሜርስ ድርጅቶች፣ ከ30 በላይ ኩባንያዎች እንዲሁም ከ50 በላይ የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች እንደሚሳተፉም ጠቁመዋል፡፡

ኤክስፖው በሣይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምርምር፣ ኢኖቬሽን፣ ዲጂታላይዜሽን እና በሥራ ፈጠራ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ለማስተዋወቅ ብሎም በአገልግሎት ሰጭና ተቀባይ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከርና ግንዛቤን ለመፍጠር ያለመ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

በመራኦል ከድር እና ሃይማኖት ወንድራድ

Exit mobile version