አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከወጪ ንግድ 772 ነጥብ 25 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ካሳሁን ጎፌ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው÷ ሚኒስቴሩ የሚከታተላቸው የወጪ ንግድ የ10 ወራት እቅድ አፈፃፀም መገምገሙን ገልጸዋል፡፡
በዚህም በ10 ወራት ከወጪ ንግድ 907 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 772 ነጥብ 25 ሚሊየን ዶላር በማግኘት የእቅዱን 85 ነጥብ 1 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል::
ለእቅዱ መሳካት ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸው የወጪ ምርቶች ቀዳሚው የቅባት እህሎች አፈፃፀም መሆኑን ገልጸው÷ 292 ነጥብ 8 ሚሊየን ገቢ በማስገኘት የእቅዱን 143 ነጥብ 5 በመቶ ማሳካቱን አመልክተዋል፡፡
በተመሳሳይ የጥራጥሬ ምርቶች 286 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር ገቢ በማስገኘት የእቅዱን 102 ነጥብ 7 በመቶ ማሳካት ችሏል ነው ያሉት::
የእንስሳት መኖና የቁም እንስሳት በገቢ የእቅዳቸውን 21 ነጥብ 8 ሚሊየን እና 16 ነጥብ 1 ሚሊየን ገቢ በቅደም ተከተል በማስገኘት አፈፃፀሙን በ100 ነጥብ 8 በመቶ እና 84 በመቶ ያሳኩ የወጪ ምርቶች ናቸው ብለዋል፡፡
የጫት የወጪ ንግድ በተደራራቢ ቀረጥ እና ኬላዎች መበራከት በውጤቱም ለኮንትሮባንድ በር በመክፈቱ ምክንያት የሚጠበቀው ውጤት ሊገኝ እንዳልቻለም ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይ ሁለት ወራት ውጤታማ ስራ ለመስራት ከፍተኛ ርብርብ እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡