አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በአሶሳ ዞን በዑራ ወረዳ አምባ 2 ቀበሌ በ53 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ወጪ ለሚገነባው አነስተኛ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።
አቶ አሻድሊ ሀሰን በክልሉ የተለያዩ አነስተኛ የመስኖ ግድቦችን በመገንባት የአርሶ አደሩን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
አዲስ የሚገነባው የመስኖ ግድብ ፕሮጀክትም 110 ሄክታር ማሳን የማልማት አቅም እንዳለው የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ 457 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የፕሮጀክቱ ግንባታ 18 ወራት እንደሚወስድ ገልፀው በጥራት እና በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅም የቅርብ ክትትል ይደረጋል ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን የአርሶ አደሩን ህይወት በዘላቂነት ለመለወጥ ያሉትን ፀጋዎች በመለየት እየተከናወኑ የሚገኙት ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል።