Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኩባ የስኳር ኢንዱስትሪ የቴክኒክ ቡድን በኢትዮጵያ ሥራ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰባት አባላት ያሉት የኩባ የስኳር ኢንዱስትሪ የቴክኒክ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ሥራ ጀምሯል፡፡

ቡድኑ ስራ የጀመረው የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ከኩባ አቻው አዝኩባ ግሩፖ አዙካሬሮ መንግስታዊ የስኳር ኩባንያ ጋር በትብበር ለመስራት በተፈራረመው የመግባቢያ ስምምነት መሠረት መሆኑ ተገልጿል።

የእርሻ፣ የፋብሪካና የምርምር ባለሙያዎችን ላካተተው የቴክኒክ ቡድን በኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የኮርፖሬት ጉዳዮች ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘመድኩን ተክሌ የሥራ መመሪያ መሰጠቱም ተመላክቷል፡፡

በወቅቱም ከቴክኒክ ቡድኑ በኢትዮጵያ የስኳር ኢንዱስትሪ ካሉበት ተግዳሮቶች ለመውጣት የሚያስችሉ የመፍትሄ ሀሳቦች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡

የቴክኒክ ቡድኑ በኢትዮጵያ የሚኖረው ቆይታ የተሳካ እንዲሆን የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ አስፈላጊውን ድጋፍ እንሚያደርግም አብራርተዋል፡፡

ለቡድኑ የኢትዮጵያን የስኳር ኢንዱስትሪ ነባራዊ ሁኔታ የትራንስፎርሜሽን ማኔጅመንት መምሪያ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ሳምሶን ወልቀባ ገለጻ አድርገዋል፡፡

የቴክኒክ ቡድኑ አባላትም በዘርፉ ያላቸውን ዕውቀትና ልምድ በመጠቀም የስኳር ኢንዱስትሪውን ከችግር ለማውጣት እንደሚሰሩ ማረጋገጣቸውን ከኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የቴክኒክ ቡድኑ በወንጂ ሸዋ፣ መተሐራ፣ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለትና ኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሦስት ስኳር ፋብሪካዎች ተዘዋውሮ እንደሚሰራ የሚጠበቅ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለትም በወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ስራ መጀመሩ ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ከኩባ አቻው አዝኩባ ግሩፖ አዙካሬሮ መንግስታዊ የስኳር አምራች ኩባንያ ጋር በትብበር ለመስራት ጥር 23 ቀን 2016 ዓ.ም የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል፡፡

Exit mobile version