Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከጾታዊ ጥቃት የጸዳች፣ ለሴቶችና ህጻናት የምትመች ሀገር ለመገንባት ሁሉም ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል- ወ/ሮ ያለም ጸጋይ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወይዘሮ ያለም ጸጋይ ከጾታዊ ጥቃት የጸዳች፣ ለሴቶችና ህጻናት የምትመች ሀገር ለመገንባት ሁሉም ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ አሳስበዋል።

የ16ቱ ቀን የፀረ ጾታዊ ጥቃት ንቅናቄ የመዝጊያ ፕሮግራም በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

ሚኒስትሯ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተፈጸሙ ባሉ ጾታዊ ጥቃቶች ሳቢያ ሴቶችና ህጻናት ለአካላዊ፣ ስነ ልቦናዊና አእምሯዊ ጉዳቶች እየተዳረጉ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም ሴቶችና ህጻናት ለበርካታ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መጋለጣቸውንም ተናግረዋል።

የሴቶች ጥቃት የሚወገዝበት የ16 ቀን የፀረ ፆታዊ ጥቃት ንቅናቄ የዘንድሮ ትኩረቱ አካል ጉዳተኛ የሆኑና ከኤች አይ ቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ ሴቶች ናቸው።

ንቅናቄው በዓለም ለ28ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ14ኛ ጊዜ “ሴቶችና ሕጻናትን ከጥቃት በመጠበቅ ኃላፊነታችንን እንወጣ!” በሚል መሪ ቃል ከህዳር 16 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ሲከበር ቆይቷል።

Exit mobile version