አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በብራዚል ደቡባዊ ሪዮ ግራንዴ ዶ ሱል ግዛት የጎርፍ አደጋ 143 የሚሆኑ ሰዎችን ህይወት ከቀጠፈ ሁለት ሳምንታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተጨማሪ የጎርፍ አደጋ ይከሰታል የሚል ስጋት መጨመሩ ተገልጿል።
ለስጋቱ መጨመር በአካባቢው የውሀ ሙላት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከፍ እያለ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
እንደ ሀገሪቱ መንግስት ገለጻ፤ ካለፈው ዓርብ ጀምሮ ሲጥል ከነበረው ከባድ ዝናብ የተነሳ ከከተማዋ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ አራት ወንዞች በከፍተኛ ሁኔታ እየሞሉ ነው፡፡
ከፈረንጆቹ ሚያዚያ 29 ጀምሮ ከባድ ዝናብ ያጋጠመው ግዛቱ፤ ክስተቱን ተከትሎ አውሎ ንፋስ፣ የመሬት መንሸራተት እና የጎርፍ አደጋ ከ538 ሺህ በላይ ሰዎችን ያፈናቀለ ሲሆን፤ 81 ሺህ የሚሆኑትን ቤት አልባ ማድረጉም ተመላክቷል፡፡
እንደገና የውሃ ሙላት ይከሰትባቸዋል ከተባሉት አራቱ ወንዞች አቅራቢያ የሚኖሩና ወደ አካባቢያቸው መመለስ ጀምረው የነበሩ ሰዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ መጠየቃቸውም ተነግሯል፡፡
ቀደም ሲል በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ተጠቂ ከነበሩ ከተሞች አንዷ የሆነችው ሙከም ከተማ ከንቲባ ማቲውስ ትሮጃን አካባቢው ለአደጋ የተጋለጠ ስለሆነ ነዋሪዎችን ከአካባቢው እያስለቀቁ እንደሆነ መናገራቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡