Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

12ኛው የአፍሪካ አቪዬሽን ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 12ኛው የአፍሪካ አቪዬሽን የባለድርሻ አካላት ጉባኤ “የአፍሪካን አቪዬሽንን ከማስተሳሰር ባሻገር” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

ጉባኤው ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን የዘርፉ ተዋናዮች ለአህጉሪቱ የአቪዬሽን መስክ መጪው ጊዜ ይዞት በሚመጣው እድል፣ በአፍሪካ አየር ትራንስፖርት ደህንነትና ኦፕሬሽን እና መሰል ጉዳዮች ላይ ይመክራል ተብሏል።

በጉባኤው የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው፣ የአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር ዋና ፀሃፊ አብዱራህማን በርቴ፣ በአፍሪካ የሚገኙ አየር መንገዶችን የሚመሩ ሃላፊዎች፣ ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር የአውሮፕላን አምራቾችና የዘርፉ ባለሙያዎች ታድመዋል።

በጉባኤው መክፈቻ ላይ ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) እንዳሉት÷ የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚን ለማንቀሳቀስ ቁልፍ ሚና አለው።

ኢትዮጵያም በተያያዘችው የኢኮኖሚ እድገት የአየር ትራንስፖርት መስክ የማይተካ ሚና እንዳለው እንገነዘባለን ነው ያሉት።

በመሆኑም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የያዘውን ሁሉን አቀፍ የአቪዬሽን መስክ የሽግግር ልህቀት ለማረጋገጥ መንግስት የበኩሉን ድጋፍ ያደርጋልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው÷ አየር መንገዱ የአፍሪካ አህጉርና የተቀረውን ዓለም በአየር ትራንስፖርት የማስተሳሰር ጉዞውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የያዘውን እቅድ እያሳካ ነው ብለዋል።

የአፍሪካ ሀገራት የአቪዬሽን ኢንዱስትሪን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር አየር መንገዶቹ ተቀራርበው መስራት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።

የአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር ዋና ፀሃፊ አብዱራህማን በርቴ÷ ጉባኤው የአፍሪካን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ተግዳሮትና ያሉ እድሎችን ለመመልከት የሚያስችል መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version