አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አንድ እናት ነፍሰ ጡር በምትሆንበት ጊዜ በርካታ ለውጦች እርግዝናዋን ተከትለው ይመጣሉ።
በመሆኑም እርግዝናን ተከትለው የሚመጡ መደበኛ ሁነቶች እንዳሉ ሁሉ በአንጻሩ ደግሞ እናትና ፅንስን ለከፋ አደጋ፤ አለፍ ሲልም ለሞት የሚዳርጉ ጤናማ ያልሆኑ ለውጦች ወይም ምልክቶች እንደሚስተዋሉ ይገለፃል፡፡
ለአብነት ከማህጸን ደም ወይም ውሃ መሰል ፈሳሽ መፍሰስ ወይም መንጠባጠብ፤ ከ37 ሳምንት በታች የሆናት ነፍሰጡር እናት ከማህጸን አካባቢ ህመም ሲሰማት ወይም ተደጋጋሚ የሆነ ከፍተኛ የቁርጠት ህመም ስሜት ከተሰማት ችግርን የሚያመለክቱ ምልክቶች ናቸው፡፡
እንዲሁም ከጊዜው በፊት የሚከሰት የምጥ ምልክቶች (ለምሳሌ ታችኛው ጀርባ አካባቢ የሚሰማ መጠነኛ ህመም፣ ዳሌ ወይም ሆድ አካባቢ የሚሰማ ጫና ወይም ክብደት ሲኖር …)፤ ድንገት የሚከሰት የፊት፣ እጅ ወይም እግር ማበጥ፣ ከፍተኛ የሆነ ሆድ ላይ የሚወጋና የሚቆርጥ ህመም፣ ከፍተኛ ራስ ምታት፣ ትኩሳት፣ ማስመለስ፣ ዐይን ብዥ ማለት፣ የፅንስ እንቅስቃሴ መቀነስ የመሳሰሉ የችግር ጠቋሚ ምልክቶች ናቸው፡፡
በዚህም አንድ ነፍሰ ጡር እናት ከላይ የተጠቀሰውን ምልክት ከተመለከተችና ከተሰማት ጊዜ ሳታባክን የህክምና ባለሙያ ጋር ቀርባ በማማከር ችግሩ ለምን እንደተከሰተ ማወቅና ተገቢውን ህክምና መውሰድ ይኖርባታል።
በጊዜ ለችግሩ መፍትሄ ካልተፈለገ ችግሩ ይወሳሰብና እናትም ልጅም ለከፍተኛ አደጋ ወይም ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችል ከአዲስ አበባ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በአጠቃላይ አንዲት ነፍሰጡር እናት በእርግዝና ወቅት የሚከሰቱ ለውጦችን ታሳቢ በማድረግ ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት መከተል፣ ተገቢ እረፍት ማድረግ፣ ለአደጋ ከሚያጋልጥ እንቅስቃሴና የሥራ ባሕሪ መራቅ፣ አደንዛዥ ዕጽና አልኮል ከመጠቀም መታቀብ ይኖርባታል፡፡