አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለጽዱ ኢትዮጵያ ዲጂታል ቴሌቶን በአንድ ጀምበር 154 ሚሊየን 500 ሺህ ብር መሰብሰቡን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
ለጽዱ ኢትዮጵያ በአንድ ጀምበር 50 ሚሊየን ብር የማሰባሰብ የዲጂታል ቴሌቶን የተጀመረው ከማለዳው ሁለት ሰአት ጀምሮ ነው።
የዲጂታል ቴሌቶኑን በርካቶች ተሳትፈውበት ምሽት 12 ሰአት ላይ የተጠናቀቀ ሲሆን ÷ከታሰበው እቅድ በላይ ማሳካት ተችሏል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ፕሬስ ሴክሬተሪያት ሃላፊ ቢልለኔ ስዩም÷በዲጂታል ቴሌቶኑ በአንድ ጀምበር 154 ሚሊየን 500 ሺህ ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል።
ከዚህም ውስጥ ከህብረተሰቡ በቀጥታ በቴሌቶኑ 67 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር መሰብሰቡን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እያንዳንዱ ዜጋ ከሚያዋጣው 3 ብር ላይ የራሱን አንድ ብር ለመጨመር በገባው ቃል መሰረት 23 ሚሊየን ብር መለገሱን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የሚድሮክ ኢንቨስትመነት ግሩፕ ሰራተኞችና በስሩ ያሉ ኩባንያዎች 64 ሚሊየን ብር መለገሳቸውን አስታውሰው በአጠቃላይ በቴሌቶኑ 154 ሚሊየን 500 ሺህ ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል።
በዲጂታል ቴሌቶኑ 40 ሺህ 533 ሰዎች መሳተፋቸውን ገልጸው ለዚህም የላቀ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በተጨማሪም በዘገባና የቀጥታ ስርጭት ተሳትፎ ለመበራቸው የሚዲያ ተቋማትም ምስጋና አቅርበዋል።