አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አትሌቶቻችን በሩጫ ከማሸነፍ ባለፈ ለውበትና ጽዳት አርአያ በመሆን የሀገራችሁን ውበት መግለጥ አለባችሁ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ለፅዱ ኢትዮጵያ በአንድ ጀምበር 50 ሚሊየን ብር የማሰባሰብ የዲጂታል ቴሌቶን ከማለዳው ሁለት ሰዓት ጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ኢሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ(ዶ/ር)ን ጨምሮ በርካታ አትሌቶች የ“ጽዱ ጎዳና – ኑሮ በጤና” ንቅናቄን ተቀላቅለዋል።
በአንድ ጀምበር 50 ሚሊየን ብር ለሰባሰብ እየተከናወነ ያለውን ዲጂታል ቴሌቶን በመቀላቀልም ድጋፋቸውን አሳይተዋል።
በዚሁ ሁነት ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)፤ የ“ጽዱ ጎዳና – ኑሮ በጤና” ንቅናቄ አላማ ገንዘብ ማዋጣት ብቻ ሳይሆን ሀገርን ንፁህ የማድረግ አላማ የሰነቀ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ አትሌቶች በአሸናፊነት የሀገራችሁን ሰንደቅ አላማ ከፍ እንዳደረጋችሁ ሁሉ ጽዱ ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ግንባር ቀደም ልትሆኑ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን በተባበረ መንገድ ያማረችና ንፁህ ሀገረ መገንባት አለብን ሲሉም መልእክታቸውን ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።