አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም ለማሳደግና ተወዳዳሪ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ተናገሩ።
በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ከተከፈተው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በተጓዳኝ “ጥናትና ምርምር ለተሻለ አቅም ግንባታ” በሚል መሪ ሐሳብ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል÷ የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም ለማሳደግና ተወዳዳሪ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም በተለይም ከትምህርት ተቋማትና በዘርፉ ከሚሰሩ ተቋማት ጋር በቅርበትና በትብብር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅምና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ዘርፉን በጥናትና ምርምር መደገፍ አስፈላጊ ስለመሆኑም አስገንዝበዋል፡፡
በእውቀትና በክኅሎት የዳበረ የሰው ኃይል በማሰማራት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የትምህርት ሴክተር ሚና የጎላ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በበኩላቸው÷ በትምህርት ጥራት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ለዘርፉ ልማት ችግር ፈቺና ቀጣይነት ያለው ጥናትና ምርምር ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡