Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም ከ1 ሚሊየን የሚልቁ ሕጻናትን መድረስ ተቻለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም በሦስት ዓመታት ውስጥ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ሕጻንትን መድረስ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

3 ሺህ 85 የወላጅና አሳዳጊ አማካሪ ባለሙያዎች የምረቃ ሥነ-ሥርዓት በወዳጅነት ዐደባባይ ተካሂዷል፡፡

በዚሁ ወቅት ከንቲባ አዳነች ባደረጉት ንግግር÷ ዛሬ የተመረቁትን ጨምሮ የወላጆች ምክር አገልግሎት ሰጪ ባለሙያዎች ቁጥር 5 ሺህ መድረሱን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ፕሮግራምም ትውልድ በመገንባት ሂደት ውስጥ ሀገር እየገነባን ነው ማለታቸውን በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡

ተመራቂዎችም ወደ ወላጆች ሲሄዱ የሚያገለግሉት ሀገርን መሆኑን አውቀው ለኢትዮጵያ መሰረት መትጋት እንዳለባቸው አሳስበው÷ ወደ ሥራ ሲሰማሩ ውጣ ውረድ ሊኖር እንደሚችል በመጠቆም ድካሙን ተቋቁመው ለሀገራቸው ሊሠሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር በሦስት ዓመታት ውስጥ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ሕጻናትን መድረስ መቻሉን ገልጸው፤ ለዚህ ስኬት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም ልምድ ለመቅሰም ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ከንቲባዎች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎችም ተገኝተዋል፡፡

Exit mobile version