አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል ሙሌት ስርዓት ረቂቅ መመሪያ ላይ ያተኮረ ውይይት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተካሂዷል።
በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የኃይል ሙሌት አገልግሎት ንግድ ላይ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ዝቅተኛ የፈቃድ መስፈርት ለመወሰንና ለኃይል ሙሌት ማዕከላት፣ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባለንብረቶች፣ ተመጣጣኝ የኃይል ሙሌት ተመን ለማውጣት ያለመ ረቂቅ መመሪያ ላይ ምክክር ተደርጓል።
የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳህረላ አብዱላሂ፤ ውይይቱ የነዳጅ አቅራቢ ተቋማት ማደያዎቻቸውን ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሙሌት ማዕከል ለመቀየር የሚያስቡ አካላትን በማቀናጀት አገልግሎት ለመስጠት በሚያስችል ሁኔታ ነው ብለዋል።
መደበኛ ያልሆኑ የኤሌክትሪክ መሙያ ጣብያዎች የሚያስከትሉት የጎንዮሽ ጉዳት ለመቆጣጠር ረቂቁ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተሞክሮ በመቅሰምና የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ያጸደቃቸውን ደረጃዎችን ማዕከል በማድረግ የሚሰራ እንደሆነም ተመላክቷል።
በታሪኩ ወ/ሰንበት