Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አዳዲስ የነዳጅ ኩባንያና የነዳጅ ማደያ መገንባት እንዲቆም የተላለፈው ውሳኔ ክትትል እንዲደረግበት ተወሰነ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አዳዲስ የነዳጅ ኩባንያ እና የነዳጅ ማደያ መገንባት እንዲቆም ቀደም ሲል በተወሰነው ውሳኔ መሰረት አፈጻጸሙ ክትትል እንዲደረግበት ኮሚቴው ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ብሔራዊ የነዳጅ ሪፎርም እስቲሪንግ ኮሚቴ ባለፉት 10 ወራት የነበረውን የነዳጅ ሪፎርም አፈጻጸም በመገምገም የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

ባለፉት 10 ወራት በታቀደው መሰረት ስራዎች መሰራታቸውን የተመለከተው ኮሚቴው በዲጂታል የነዳጅ ግብይት የሚካሄደውን መረጃ በማዕከል ለማደራጀት እየተጠና ያለው ሲስተም ልማት እየተጠናቀቀ መሆኑን ገምግሟል፡፡

የነዳጅ ስርጭትን ከግዥ ትዕዛዝ ጀምሮ ከወደብ ከተጫነ በኋላ ማደያ እስኪራገፍ ድረስ ያለውና ከተራገፈ በኋላ የነዳጅ ስርጭቱ በዲጂታል መፈፀሙን ኦዲት ለማድረግ የሚያስችል ሲስተም ጥናት ተጠናቆ ወደ ሙከራ ትግበራ መግባት መቻሉም ተመላክቷል፡፡

እስካሁንም የታለመለት የነዳጅ ድጎማን ያለአግባብ የወሰዱ ተሽከርካሪዎች ላይ ኦዲት በማድረግ እርምጃ መውሰድ መጀመሩ በጠንካራ አፈጻጸም ገምግሟል።

እንዲሁም አሁን ያለው የነዳጅ ሪፎርም ተጠናክሮ መቀጠሉ በነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ ላይ የነበረውን ከፍተኛ የዕዳ ጫና ወደ 89 ቢሊየን ዝቅ ማድረጉ በጥንካሬ የተገመገመ ሲሆን÷ ያልተጠናቀቁ ስራዎችም በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ሲል ኮሚቴው አሳስቧል።

አዳዲስ የነዳጅ ኩባንያና የነዳጅ ማደያ መገንባት እንዲቆም ቀደም ሲል በተወሰነው ውሳኔ መሰረት አፈጻጸሙ ክትትል እንዲደረግበት መወሰኑም ተመላክቷል፡፡

እንዲሁም የተሽከርካሪ ሰሌዳ ምዝገባ አዲስ በሚለማው የተሽከርካሪ መረጃ ማዕከል እንዲደራጅ ሲል ኮሚቴው ውሳኔ ማሳለፉን ከነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

Exit mobile version