የሀገር ውስጥ ዜና

የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ የትግበራ ምዕራፍ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው

By Amele Demsew

May 09, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ የትግበራ ምዕራፍ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

በመርሐ ግብሩ ፖሊሲውን ከማስተግበር አንጻር በቀጣይ ስለሚከናወኑ ስራዎች ምክክር እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል።

በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀው የሽግግር ፖሊሲ፣ የኢትዮጵያን አውድ መሰረት ያደረገ የተቀናጀ እና የተናበበ የሽግግር ፍትሕ ሂደት የሚመራበት እና የሚተገበርበትን ሥርዓት የመዘርጋት ዓላማ እንዳለው ተነግሯል።

ዘላቂ ሰላም፣ ዕርቅ፣ የህግ የበላይነት፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ የሚረጋገጥበት መደላድል መፍጠርም የፖሊሲው ሌላኛው ዓላማ እንደሆነ ተመላክቷል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት በመርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ አንድ ማህበረሰብ ላለፈበት ከባድ ፈተና እና በደል ፍትህን ለማምጣትና እርቅን ለማውረድ የሚተገበር ነው ብለዋል።

የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ አሰራር ላለፉ በደሎችን ፍትህ ማሰጠት እና ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንዲሁም ሁሉን አቀፍ ምላሽ መስጠት እንደሆነም አንስተዋል።

ፖሊሲውን ለማርቀቅ በፍትሕ ሚኒስቴር ስር የተቋቋመው የባለሙያዎች ቡድን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ውይይቶችን ማካሄዳቸው ተገልጿል።

በሂደቱ የተሳተፉ አካላት ሊመሰገኑ እንደሚገባ ገልጸው፤ እገዛቸው ቀጣይ እንዲሆን የፍትህ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) አንስተዋል።

በይስማው አደራው