ቴክ

ዓለም አቀፉ የዲጂታል ማዕቀፍ የአፍሪካን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ አግባብ ሊዘጋጅ ይገባል ተባለ

By Shambel Mihret

May 09, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የዲጂታል ማዕቀፍ የአፍሪካን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ አግባብ ሊዘጋጅ እንደሚገባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴዔታ ይሹሩን አለማየሁ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባዘጋጀው ዓለም አቀፍ የዲጂታል ማዕቀፍ ረቂቅ ሰነድ ላይ ዳታን ያማከለ ውይይት በአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ ይሹሩን አለማየሁ (ዶ/ር)÷ዓለም አቀፉ የዲጂታል ማዕቀፍ አካታችነትን፣ ተደራሽነትን እና ደህንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል መጻኢን እውን ማድረግን በግብነት ያስቀመጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በዲጂታል ልማት ላይ እየሰራችው ያለው ሥራ በዓለም አቀፉ የዲጂታል ማዕቀፍ ረቂቅ ሰነድ ውስጥ ከተቀመጡት አላማዎች እና የግብ ማስፈጸሚያ ክላስተሮች ጋር የተጣጣመ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በውይይቱ የዓለም አቀፉ የዲጂታል ማዕቀፍ ተባባሪ አዘጋጅ የሆኑት የስዊድን እና ዛምቢያ አምባሳደሮች፣ የተመድ የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን የሴክሽን ሃላፊ፣ የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ከዓለም አቀፍ ተቋማትና ሀገራት የተወከሉ ባለሙያዎች መሳተፋቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡