አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሃማስ በግብጽ እና ኳታር የቀረበውን የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት የውሳኔ ሃሳብ መቀበሉን አስታውቋል።
ውሳኔው የእስራኤል ጦር በምሥራቅ ራፋህ የሚገኙ 100 ሺህ በላይ ዜጎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ማሳሰቡን ተከትሎ የተወሰነ ነው ተብሏል፡፡
የሃማስ መሪ እስማኤል ሃኒዬህ እንደገለጹት÷ሃማስ የተኩስ አቁም ስምምነት የውሳኔ ሃሳቡን መቀበሉን የሚገልጽ መልዕክት ለግብጽ እና ኳታር አደራዳሪዎች ተልኳል፡፡
ይሁን እንጂ በጋዛ እንዲደረግ የቀረበው የተኩስ አቁም ስምምነት የውሳኔ ሃሳብ ያካተታቸው ዝርዝር ጉዳዮች አለመጠቀሳቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል የተኩስ አቁም ስምምነቱ ታጋቾች እንዲለቀቁ እና ለ42 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ የሚሉ ሃሳቦችን ሊያካትት እንደሚችል ተመላክቷል፡፡
የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን ሃማስ በግብጽና ኳታር የቀረበውን የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት የውሳኔ ሃሳብ መቀበሉን አድንቀዋል፡፡
እስራኤል ተመሳሳይ ውሳኔ እንደምታሳልፍ እምነታቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡