ስፓርት

ጁለን ሎፔቴጉይ የዌስትሃም አሰልጣኝ ለመሆን ተስማሙ

By Mikias Ayele

May 06, 2024

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ስፔናዊው አሰልጣኝ ጁለን ሎፔቴጉይ በውድድር ዓመቱ መጨረሻ የዌስትሃም ዩናይትድ አሰልጣኝ ለመሆን ተስማምተዋል፡፡

ስምምነቱ ተፈጻሚ ከሆነም የ57 ዓመቱ የቀድሞ የዎልቭስ አሰልጣኝ በድጋሚ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ እንደሚመለሱ ይጠበቃል፡፡

የመዶሻዎቹ አለቃ ዴቪድ ሞይስ ዌስትሃም ባለፉት 9 ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ብቻ ማሸንፉ እና ከዩሮፓ ሊግ ውጪ መሆኑን ተከትሎ ጫና ውስጥ ገብተው ቆይተዋል፡፡

በዚህ ክረምት የኮንትራት ውላቸው የሚጠናቀቀው ዴቪድ ሞይስ የክለብ ቆይታቸውን በተመለከተ የፊታችን ግንቦት 19 ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ከሚያደርጉት ጨዋታ በኋላ ንግግር እንደሚጀመሩ ገልጸው ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ትላንት ምሽት በቼልሲ የ5 ለ 0 ሽንፈት ያጋጠማቸው አሰልጣኙ÷ ጁለን ሎፔቴጉይ ከዌስትሃም ጋር የሚፈራረሙ ከሆነ ከመዶሻዎቹ አሰልጣኝነት በይፋ የሚሰናበቱ ይሆናል፡፡

የቀድሞ የስፔን እና የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ የነበሩት ጁለን ሎፔቴጉይ ከወልቭስ አሰልጣኝነት ከተሰናበቱ በኋላ ድጋሚ ወደ እንግሊዝ ለመመለስ ፍላጎት እንደነበራቸው ሲገልጹ መቆየታቸውን ቢቢሲ ስፖርት አስነብበቧል፡፡