Fana: At a Speed of Life!

የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገቡ ነው – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገቡ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ተካሂዷል፡፡

በዛሬው ዕለትም የኑሮ ውድነትን ከማረጋጋት፣ ከስራ ዕድል ፈጠራ እና የተረጂነት አመለካከትን ከመለወጥ አኳያ በተሰሩ ስራዎች ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱም ፓርቲው በሱፐርቪዢን ምልከታ እና በሌሎችም ጊዜያት በተደረጉ የውይይት መድረኮች ከህዝቡ የተነሱ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመመለስ እየሰራ መሆኑ ተጠቁሟል።

ለአብነትም የምርት አቅርቦትን ከማሻሻል፣ የኑሮ ውድነትን ከማረጋጋትና የዋጋ ንረትን ከመቆጣጠር አንጻር የተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤቶች እያስገኙ መሆኑ ተመላክቷል።

አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት÷ ህዝቡን እየጎዳ የሚገኘውን የኑሮ ውድነት ለመቆጣጠር በመንግሥት እና በፓርቲ በኩል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በሀገር ደረጃ በርካታ ኢንሼቲቮች ተቀርጸው ወደ ስራ በመገባቱ ምርትና ምርታማነት እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው÷ የንግድ ሰንሰለቱን በማሳጠር አምራችን ከሸማቹ ለማገናኘት የተሰሩ ስራዎችም ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገቡ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የተረጂነት አመለካከትን ከመለወጥ አኳያ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የጠቆሙት የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳነት÷ የመስራት አቅም ያላቸው ዜጎች ሰርተው መለወጥ እንዲችሉ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
የምግብ ዋስትናን እና የኢኮኖሚ ነጻነትን ማረጋገጥ መቻል የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ትልቅ አቅም መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ባቀረቡት የመወያያ ጽሑፍ÷ ከስራ ዕድል ፈጠራ አንጻር በበጀት ዓመቱ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

በሀገር ደረጃ እየተተገበሩ የሚገኙ ኢኒሼቲቮች የስራ ዕድል መፍጠሪያ በማድረግ አበረታች ስራዎች መከናወናቸውንም ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ ከስራ ዕድል ፈላጊዎች ቁጥር አንጻር በቀጣይ ጊዜያት ሰፊ ስራዎችን መሰራት እንደሚገባ ጠቁመው ከስራ ዕድል ፈጠራ አንጻር የአመለካከት፣ የክህሎት፣ የግብዓት እና ሌሎች ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የተረጂነት አመለካከቶችን ማስወገድ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ዜጎች በአካባቢያቸው ስርተው እንዲለወጡ የሚያግዙ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመው ይህም በተለያዩ አካባቢዎች እየተሰራ እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ÷ አምራቾችን ከሸማቾች ጋር ለማገናኘት በተሰሩ ስራዎች በርካታ የገበያ ማዕከላት ተቋቁመው አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በሀገር ደረጃ አሁን ላይ 970 የእሁድ ገበያዎች መቋቋማቸውን ጠቁመው የኑሮ ውድነቱን ከማረጋጋት አንጻር ትልቅ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በውይይቱ ሃሳባቸውን የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ÷ የዋጋ ግሸበትን በመቀነስ የተረጋጋ የኑሮ ሁኔታ እንዲፈጠር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ምርታማነትን ማሳደግ እንዲሁም የተመረተውን ምርት በአግባቡ ለገበያ ማቅረብ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ በመሆኑ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ተናግረዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.