Fana: At a Speed of Life!

ከዳያስፖራው 3 ቢሊየን ዶላር በሬሚታንስ ወደ ሀገር መላኩ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከዳያስፖራው የሚገኘውን ሬሚታንስ ለማሳደግ በተደረገ ድጋፍና ክትትል 3 ቢሊየን ዶላር የሬሚታንስ ገቢ መገኘቱን የዳያስፖራ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

በዳያስፖራ ዘርፍ የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈፃፀም ላይ ከኢፌዴሪ ሚሲዮኖች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱም ባለፉት 9 ወራት ከ197 ሺህ በላይ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላትን ያሳተፈ ወቅታዊና ሀገራዊ የልማት ጉዳዮች የተዳሰሱባቸው ከ730 በላይ የዙምና የገጽ ለገጽ መድረኮች መካሄዳቸው ተነስቷል፡፡

ወጣት የዳያስፖራ አባላት ለሀገራዊ ጥሪ በጎ ምላሽ እንዲሰጡ በተደረገው ጥረት በመጀመሪያው  ዙር ብቻ ከ75 ሺህ በላይ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት መግባታቸው ተገልጿል።

የዳያስፖራውን የልማት ተሳትፎ ለማሳደግ በተከናወነው ሥራ 1 ሺህ 166 የዳያስፖራ አባላት በንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሳተፉ በማድረግ ለ1ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩ ተጠቅሷል፡፡

4 የዳያስፖራ አባላትንና አደረጃጀቶችን በማሳተፍና በማስተባበር በቴክኖሎጂ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በደህንነትና ጥበቃ፣ በፋርማሲ ማኑፋክቸሪንግ፣ በትምህርትና በስልጠና ዘርፎች የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር መካሄዱ ተጠቁሟል፡፡

ባለፉት 8 ወራት ብቻ 17 ቢሊዮን ብር ካፒታል  ያስመዘገቡ1 ሺህ 745 የዳያስፖራ አባላት የውጭ ምንዛሬ አካውንቶችን ከፍተው ከ2 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር በላይ ተቀማጭ  ማድረጋቸውም ተጠቅሷል፡፡

ከዳያስፖራ የሚገኘውን ሬሚታንስ ለማሳደግ በተደረገው ድጋፍና ክትትልም 3 ቢሊየን ዶላር መላኩ ተገልጿል።

ለህዳሴ ግድብ ግንብታ ከ410 ሺህ ዶላር በላይ፣ ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላር እንዲሁም ለልዩ ልዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ከ17 ሚሊየን ዶላር በላይ በጥሬ ገንዘብና በአይነት ድጋፍ ማሰባሰብ መቻሉ ተመላክቷል፡፡

ይህም በሬሚታንስና በኢንቨስትመንት የተገኘውን ሃብት ሳይጨምር ባለፉት 9 ወራት ከዳያስፖራው የተሰባሰበውን የድጋፍ መጠን ከ18 ሚሊየን ዶላር በላይ ደርሷል መባሉን የአገልግሎቱ  መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.