አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተገኘውን ሠላም ለማጠናከር እና ሥር ለማስያዝ በርካታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንገኛለን ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ገለጹ።
በክልሉ የተገኘውን ሰላም ዘላቂነት አጽንቶ ማስቀጠልን ያለመ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሉት÷ በክልሉ አጋጥመው የነበሩ የፀጥታ ችግሮች በሠላማዊ ውይይትና ድርድር ለመፍታት የክልሉ መንግስት ረዥም ርቀት ተጉዟል፡፡
በዚህም አዎንታዊ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉን አስታውሰው፤ አሁን ላይ የተገኘውን አንፃራዊ ሠላም ለማጠናከር እና ሥር ለማስያዝ በርካታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡
ለዚህም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ትጥቅ የማስፈታት እና የመልሶ ማቋቋምን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ጠቁመው፤ ባለድርሻ አካላት እያደረጉት ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
የክልሉ ሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አብዱሰላም ኢብራሂም በበኩላቸው÷ አጋጥመው የነበሩ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት ከሀይል ይልቅ የሠላም አማራጭን በማስቀደም አንፃራዊ ሠላም መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
የተገኘውን ሠላም በዘላቂነት ጠብቆ ለማስቀጠል የሁሉም ባለድርሻ እገዛ እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውን ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡