አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ አካባቢዎች በበልግ ዝናብ ምክንያት ከባድ ጉዳት እንዳይደርስ የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ገለጹ።
በኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ትንበያ መሰረት ዘንድሮ በልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊያጋጥም ይችላል።
በእነዚህ አካባቢዎች በጎርፍ ምክንያት ዜጎች ጉዳት እንዳይደርስባቸው በአካባቢዎቹ የቅድመ ጥንቃቄና የመከላከል ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ በየደረጃው ግብረ ሃይል ተደራጅቶ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ በሚያስከትለው ጎርፍ ሳቢያ መንገዶች ላይ ጭምር ጉዳት ሊደርስ ስለሚችል የግብርና ግብዓቶችና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች ቀድሞ እንዲደርስ መደረጉንም ጠቁመዋል።
በወንዝ ዳርቻ አካባቢ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከክልሎች ጋር በመቀናጀት ወደ ሌላ አካባቢ የማስፈር እንዲሁም ተከታታይ ክትትልና ቅኝት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
በተደጋጋሚ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የፌዴራል መንግስት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ማስታወሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በተያያዘም የበልግ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ መምጣቱን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ለምርትና ምርታማነት ማዋል እንደሚገባም አክለዋል።