አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ1 ቢሊየን ዶላሩ ባለዕድለኛ ገንዘቡን ጎበዝ ሃኪም እንዲኖረኝ እጠቀምበታለሁ ሲል ተሰምቷል፡፡
ቼንግ ቻሊ ሳኢፋን የተባለው የ46 ዓመት ጎልማሳ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነው፡፡
የኦሪገን ነዋሪው ሰኢፋን ለሥምንት ዓመታት በካንሰር ህመም ሲሰቃይ የቆየና ጤናው እንዲመለስ ብርቱ ጥረት እያደረገ የሚገኝም ነው፡፡
ሆኖም ጤና ማጣት ከህመም ስሜቱ በተጨማሪ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ሁኔታን በመፈተን ተጨማሪ ፈተና እንደሚጋርጥ የታወቀ ነው፡፡
ሳኢፋንም የካንሰር ህመሙን ሲያስታምም እየተቆጠሩ ያሉ ዓመታትን ይገታልኛል ያለው ዕድል በሩን አንኳክቶታል ነው የተባለው፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው ፤ ሳኢፋን እና ጓደኛው ሎተሪ የመቁረጥ ሃሳብ ሹክ አላቸው፤አፍታም ሳይቆዩ ተያይዘው ሎተሪውን በመዋጮ ይቆርጣሉ፡፡
ጓደኛው በዛው ቀን የሎተሪውን ምስል ለሰኢፋን ስትልክለት ፥ “ቢሊየነሮች ነን” ከሚል ቀልድ አዘል ማጀቢያ ጽሁፍ ጋር አይይዛ ነበር፡፡ ሆኖም የብስራት ዜና ይመጣል ብሎ የጠበቀ የለም፡፡ ግን ሆነ፡፡
በማግስቱ ሰኢፋን ወደስራ ስትሄድ ለነበረችው ጓደኛው የእጣውን ቁጥር ይዞ ነበርና “ከእንግዲህ ወደስራ መሄድ አይጠበቅብሽም” ሲል የብስራቱን ዜና አጋርቷታል ነው የተባለው፡፡
ሰኢፋን ይህን አስመልክቶ ሲናገር ፥ ሎተሪውን ከቆረጥን በኋላ “እርዳታ እፈልጋለሁ ፤ ለቤተሰቤ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሳላሟላ አልሙት” ብዬ ጸሎቴን አድርሼ ነበር ብሏል፡፡
ሳይውል ሳያድር ጸሎቱ የተሰማለት ጎልማሳው ሰኢፋን ፥ ዕድሉ ወትሮውም ቢሆን ለዓመታት የያዘውን ተስፋ ገሃድ ያወጣ ብስራት ሆኖለታል ነው የተባለው፡፡
በዚህም ሰኢፋንና ጓደኛው ገንዘቡን ለሁለት እንደሚካፈሉት የተገለጸ ሲሆን ፥ ከታክስ ውጪ 422 ሚሊየን ዶላር ለእያንዳንዳቸው እንደሚደርሳቸው ተነግሯል፡፡
በዚህም በካንሰር እየተሰቃየ ያለው ሰኢፋን ገንዘቡን ማለፊያ የሆነ ሃኪም እንደሚቀጥርበትና ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡
የ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላሩ ይህ እድል በታሪክ ከፍተኛ ረብጣ ገንዘብ ካስገኙት ውስጥ የሚመደብ ነው መባሉን የዘገበው ስካይ ኒውስ ነው፡፡