Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የብልጽግና ፓርቲ የ9 ወር የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሦስት ቀናት የሚቆየው የብልጽግና ፓርቲ የዘጠኝ ወር የሥራ አፈፃፀም የግምገማ መድረክ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህን ጨምሮ የዋና ጽሕፈት ቤቱ የዘርፍ ኃላፊዎች እና የክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች በመድረኩ ላይ ተገኝተዋል፡፡

ቅቡልነት ያለው የሀገረ-መንግሥት ሥርዓት ለመገንባት፣ የሕዝቡን ተሳትፎ፣ ተጠቃሚነትና እርካታ ለማረጋገጥ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በየደረጃው በሚገኙ የፓርቲው መዋቅሮች በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን አቶ አደም በመድረኩ ላይ ገልጸዋል፡፡

በመድረኩም የውስጠ ዴሞክራሲ ባህል ደረጃ፣ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት፣ ባለፉት ስድስት ዓመታት የተገኙ የለውጥ እምርታዎችና በምርጫ ማግስት ፓርቲው ለሕዝቡ ቃል የገባቸው ጉዳዮች የተፈፃሚነት ደረጃ ትኩረት እንደሚደረግባቸው ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም በአምስቱ ሀገራዊ የልማት የትኩረት መስኮች የተገኙ ውጤቶች፣ የብሔራዊነት ትርክትን እንደ ሀገር ለመገንባት የተሄደባቸው ርቀቶች እንዲሁም የ2ኛ መደበኛ ጉባዔ ዝግጅትም ትኩረት ይደረግባቸዋል ብለዋል፡፡

መድረኩ የፓርቲውን አፈፃፀም በጋራ በመገምገም ያለበትን ደረጃ ለመለየትና የተግባራትን ስኬታማነት በቀጣይ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚያግዝም ነው ያስረዱት፡፡

እንዲሁም ውጤታማ የክትትልና ድጋፍ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ይረዳል ማለታቸውን ከፓርቲው የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡

በዘርፎች የተከናወኑ የዘጠኝ ወራት ሪፖርት፣ የተጠናቀቁ የፓርቲ መመሪያዎች እንዲሁም የ2017 በጀት ዓመት ቅድመ ዝግጅት መነሻ አቅጣጫዎችም በመድረኩ እንደሚቀርቡ ተጠቅሷል፡፡

Exit mobile version