Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የፍትህ ስርዓቱን ለማንቃት የዜጎችን ተሳትፎ ማጎልበት ይገባል- አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፍትህ ስርዓቱን ለማንቃትና የህግ የበላይነትን ለማስከበር የዜጎችን ተሳትፎ ማጎልበት እንደሚገባ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋንቱ ተስፋዬ ተናገሩ።

በአማራ ክልል የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ጥምር ኮሚቴ በጎንደር ከተማ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር እየተወያየ ነው።

በዚሁ ወቅት የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋንቱ ተስፋዬ÷የፍትህ ስርዓቱን ለማንቃትና የህግ የበላይነትን ለማስከበር የዜጎችን ተሳትፎ ማጎልበት ይገባል ብለዋል፡፡

በክልሉ የፍትህና የዳኝነት ስርዓት ላይ እያጋጠሙ ያሉ እንከኖች መንስኤ ምን እንደሆነ ለመለየት ጥረት መደረጉንም አንስተዋል፡፡

ተቋማቱን ለማጠናከርና የፍትህ ተደራሽነትን ለማስፋት ማህበራዊ እሴቶችን በማካተት መስራት ያስፈልጋልም ነውያሉት፡፡

በክልሉ የዳኝነት አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አቡየ ካሳሁን ናቸው፡፡

ከአገልግሎት ተደራሽነት አኳያ በአሁኑ ሰአት በክልሉ 7 ዞኖች የተደራጀ የፍርድ ቤት ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን በመግለጽ ከዳኝነት ስነ ምግባር ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን ለማስተካከልም ጥረት እንደሚደረግ አመላክተዋል፡፡

የጎንደር ከተማ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሀላፊ አቶ ግርማይ ልጃለም በበኩላቸው÷በቅርቡ የተጀመረው የከንቲባ ችሎት ለህብረተሰቡ ተስፋ የሰጠ በመሆኑ በክፍለ ከተሞችም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይደረጋል ብለዋል።

በሙሉጌታ ደሴ

Exit mobile version