Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኢ-ኮሜርስ ስትራቴጂ ረቂቅ ሠነድ ላይ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በብሔራዊ የኢ-ኮሜርስ ስትራቴጂ ረቂቅ ሠነድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ እያካሄደ ነው።

በመድረኩም÷ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የንግድና ቀጣናዊ ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላን (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በመድረኩ እንዳሉት፤ ረቂቅ ስትራቴጂክ ሠነዱ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የገበያ ትስስር በመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው ወሳኝና ሠነድ ነው።

ረቂቅ ሠነዱ ሀገራዊ የልማት ፕሮግራምን የማሳደግ፣ ለኢኮኖሚ እድገትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነትን የመፍጠር ዓላማ እንዳለው ጠቁመዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ሚኒስትሩ ገ/መስቀል ጫላ በበኩላቸው ዓለም የዲጂታል አብዮት እያካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከነዚህም መካከል የኤሌክትሮኒክስ ንግድ ወይም ኢ-ኮሜርስ አንዱ እንደሆነ ተናግረዋል።

በአንድ ሀገር የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማትን ማፋጠን የሚቻለው ለዘርፋ አስቻይ የሆነ የህግና የቁጥጥር ማዕቀፍ ሲኖር መሆኑንም አስገንዝበዋል።

የኢ-ኮሜርስ ስትራቴጂ÷ ዘርፉ የሕግ ማዕቀፍ ኖሮት ተወዳዳሪ ከማድረግ ባሻገር የዲጂታል ኢትዮጵያን ሽግግር ለማሳለጥ ማለሙ ተገልጿል።

በበረከት ተካልኝ

Exit mobile version