Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በአማራ ክልል የሚገኙ የልማት ስራዎችን ለማጠናከር ሰላም አስፈላጊ ነው – ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የሚገኙ የልማት ስራዎችን ለማጠናከር ሰላም አስፈላጊ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የተመራ የፌደራል መንግሥት እና የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ልዑክ የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎብኝቷል፡፡

ጉብኝቱን አስመልክቶ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ÷ በህልውና ጦርነቱ የኢንዱስትሪ መንደሮቿን ጨምሮ የከፋ ጉዳት የደረሰባት የኮምቦልቻ ከተማ በተገኘው ሰላም ወደ ቀደመ ድምቀቷ መመለሷን ዛሬ ተመልክተናል ብለዋል።

በጉብኝቱ የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ አምራች ድርጅቶች ከክልሉ አልፎ ለሀገር እድገት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸውን ምርቶች በሙሉ አቅም እና ጥራት እያመረቱ እንደሆነ መመልከታቸውን ገልፀዋል።

ምርቶቹ በከፍተኛ ጥራት ተመርተው ወደ ውጭ የሚላኩ ናቸው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ በቀጣይ የሀገር ውስጥ ገበያውን ይቀላቀላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል፡፡

መንግስትም ለሀገር ውስጥ ምርት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም ነው የተነሳው።

ስራ ከድህነት የምንወጣበትና ደማቁን የአሸናፊነት ታሪካችንን በደማቁ የምመንጽፍበት መሳሪያችን ነው ያሉት አቶ ተመስገን ÷ ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ ሰላም ቁልፉ መንገድ መሆኑን ነው የገለፁት።

በዚህም በአጭር ጊዜ ወደ ስራ የተመለሰው የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክም ሆነ ሌሎች የክልሉ የልማት ስራዎችን ለማጠናከር ሰላም ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በአማራ ክልል ጥያቄዎችን ከሰላም ውጭ በመሳሪያ ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሰው ሃይል ወደ ውይይትና ምክክር እንዲመለስ ከፌደራል መንግስትም ሆነ ከክልሉ የቀረበውን ጥሪ እንዲጠቀምም አሳስበዋል፡፡

ከሰላሞ እና ከውይይት ውጭ በጠመንጃ ጥያቄን ለማስመለስ የሚደረግ ሙከራ የክልሉን ልማት ወደኋላ የሚመልስ፣ የማይሳካና አክሳሪ በመሆኑ ይህን ለማስቆም የፌደራልም ሆነ የክልሉ መንግስት ህግና ስርዓትን ለማስከበር የጀመረውን ስራ እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል፡፡

Exit mobile version