አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ባለፉት 9 ወራት ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 112 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሎው ኡቡፕ (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ ባለሃብቶቹ ፈቃዱን የወሰዱት በግብርና፣ በማዕድን፣ በአገልግሎትና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመሰማራት ነው።
በበጀት ዓመቱ የነበረው የኢንቨስትመንት ፍሰት ከቀደሙት ዓመታት ጋር ሲነፃጸር መጠነኛ መቀነስ የታየ ቢሆንም ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ሲታይ አበረታች መሆኑን ነው የተናገሩት።
ፈቃድ ከወሰዱት ባለሃብቶች መካከል 96ቱ በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚሰማሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በግብርና ኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፈቃድ የወሰዱ 35 ባለሃብቶች ከ38 ሺህ 270 ሄክታር በላይ የእርሻ መሬት ተረክበው ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቁመው፤ ቀሪዎቹ በሒደት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ማዕድንን ጨምሮ በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ፈቃድ የወሰዱት 16 ባለሃብቶች የመስሪያ ቦታ ተረክበው ወደ ስራ ገብተዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡