አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኖርዌይ ኦስሎ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራዊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኖቤል ሽልማትን በማግኘታቸው ደስታቸውን በሰልፍ ገለፁ።
ኢትዮጵያዊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክትር ዐቢይ ባረፉበት ግራንድ ሆቴል ተገኝተው ነው ደስታቸውን የገለፁት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይም ደስታቸውን ለመግለፅ በሆቴሉ ለተገኙ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን ምስጋና እና ሰላምታ አቅርበዋል።
ዶክተር ዐቢይ በትናትናው ዕለት የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማታቸውን ኦስሎ በተካሄደው ስነ ስርዓት መቀበላቸው የሚታወስ ነው።
በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር “ሰላም እንደ ዛፍ ችግኝ ነው፤ ችግኝን ተክሎ ለማሳደግ እንክብካቤ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ሰላምም ጥሩ ልብ እና እንክብካቤ ያስፈልገዋል” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማቱን በሀገራቱ መካከል ሰላም እንዲመጣ ዋጋ በከፈሉ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ስም እንዲሁም ለኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ስምምነት ቁርጠኛ በነበሩት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ስም እንደሚቀበሉ መናገራቸው የሚታወስ ነው።
Photo Credit: Jo Straube