ጤና

በአፍሪካ ክትባት ከ50 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ሕይወት መታደጉ ተገለጸ

By Meseret Awoke

April 25, 2024

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ ህጻናት ላይ ትኩረት ያደረገ የክትባት ዘመቻ ባለፉት 50 ዓመታት 51 ነጥብ 2 ሚሊየን የሚገመቱ ሰዎችን ሕይወት መታደግ መቻሉን የዓለም ጤና ድርጅት ገለጸ።

በፈረንጆቹ 1974 የተጀመረው የዓለም ጤና ድርጅት ኢኒሼቲቭ ለሁሉም ሕፃናት ሕይወት አድን የሆኑ ክትባቶችን ለማዳረስ በተከፈተው የክትባት ፕሮግራም (ኢፒአይ) ሥር የኩፍኝ በሽታን ጨምሮ ገዳይ በሽታዎችን ለመከላከል በመደበኛነት እንዲከተቡ ማድረግ መቻሉን የዓለም ጤና ኤጀንሲ አስታውቋል።

“በበሽታ መከላከያ ክትባቶች ምክንያት አሁን ላይ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በሕይወት እና በጤና ይገኛሉ” ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ክልላዊ ዳይሬክተር ማትሺዲሶ ሞኢቲ ተናግረዋል።

የአፍሪካ ሀገራት ለህጻናት ሞት ዋነኛ መንስኤ የሆኑትን ተላላፊ በሽታዎች ለማጥፋት የክትባት አቅርቦትን ማስፋት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ብዙ የአፍሪካ ሀገራት በክትባቶች መከላከል ለሚቻሉ 13 በሽታዎች ከመጀመሪያዎቹ 6 ዓመታት ጀምሮ ለሚገኙ ህጻናት እየተሰጠ መሆኑን አንስተው ፥ ይህም በተቋማት በሚደረገው የማያቋርጥ ድጋፍ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

እንደ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ባለፉት 22 ዓመታት በአፍሪካ 19 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚገመቱ ሰዎችን ሞት መከላከል ችሏል ፤ በዚህ ምክንያትም የማጅራት ገትር በሽታ ሞት በ39 በመቶ ቀንሷል።

በተጨማሪም በፈረንጆቹ 2022 አህጉሪቱ ሁሉንም ህጻናት ለመከተብ ያላሰለሰ ጥረት ከሀገር በቀል የፖሊዮ ቫይረስ ነፃ መሆኗ በተነገረበት ወቅት የእናቶች እና ጨቅላ ህጻናት ቴታነስ በአፍሪካ በተፋጠነ የክትባት ሂደት ሊጠፋ መቃረቡ ተመላክቷል፡፡

የማህፀን በር ካንሰርን የሚያመጣው ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስና ወባ ክትባት መጀመሩ በህፃናት፣ ሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የሚደርሰውን ሞት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ ድርጅቱ መግለጹን የዘገበው ሺንዋ ነው፡፡

ክትባትን ለማስቀጠል የአፍሪካ ሀገራት ከተሳሳተ መረጃ ጋር የተገናኘውን ጥርጣሬ ከሥር መሰረቱ ለማጥፋት መሠረተ ልማት፣ የሰው ኃይል እና የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ አለባቸውም ተብሏል፡፡