አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የታክስ ሕግ ተገዥነት ንቅናቄና የግንባር ቀደም ግብር ከፋዮች እዉቅና እና ሽልማት መድረክ በቡታጅራ ከተማ ተካሄደ::
“ከየካቲት እስከ የካቲት ግብር ለሀገር ክብር” በሚል መሪ ሀሳብ የታክስ ሕግ ተገዥነት ንቀናቄ ማጠቃለያ መርሐ ግብር የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰውን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል::
በአዲስ ምዕራፍና በአዲስ ተስፋ የገቢ አቅምን በማሳደግ ለሀገር እድገት መስራት እንደሚገባ በመድረኩ ተገልጿል ::
ለታክስ ሕግ በመገዛት በታማኝንት ግብር መክፈል እንደሚገባና ለሀገር እድገት በጋራ መስራት እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡
ለህግ ተገዢና ታማኝ ግብር ከፋይ ለሆኑ የክልሉ ግብር ከፋዮች እዉቅና እና ሽልማት መስጠት እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ዘይኔ ቢልካ እንደገለጹት÷ “በአዲስ ምዕራፍ፣ አዲስ ተስፋ ለአዲስ ክልል” በሚል መሪ ሃሳብ የገቢ አቅምን ማሳደግ እና የገቢ ተቋሙን የማሻሻል ሥራ ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
በክልሉ የታክስ ህግ ተገዢነት የተጠናከረ እንዲሆን በሰባቱም የክልል ማዕከል ከተሞች ላይ ለደረጃ” ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች የንቅናቄ መድረክ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በክልሉ ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር 95 በመቶ የሚሆኑት ግብር ከፋዮች ደረሰኝ አይቆርጡም ነበር ያሉት አቶ ዘይኔ ÷ይህ አሃዝ አሁን ወደ 50 በመቶ ዝቅ ማለቱን አንስተዋል።
በክልሉ ባለፉት 9 ወራት 8 ቢሊየን 36 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ገልጸው ÷ለህግ ተገዢ ባልሆኑ 318 ግብር ከፋዮችላይ የ50 ሺህ ብር ቅጣት መተላለፉን ተናግረዋል፡፡
በኦሊያድ በዳኔ