አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሪያ ፋውንዴሽን ፎር ኢንተርናሽናል ሄልዝ በጤናው ዘርፍ ለኢትዮጵያ እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ጠየቁ፡፡
ሚኒስትሯ ከኮሪያ ፋውንዴሽን ፎር ኢንተርናሽናል ሄልዝ ዳይሬክተር ጆንግሶህ አህን ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ድርጅቱ እያደረገ ላለው ድጋፍ ያመሰገኑት ዶ/ር መቅደስ÷ በተለይም የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራቱ ከጤና ሚኒስቴር ዓላማ ጋር የተጣጣመ ሆኗል ብለዋል፡፡
ድርጅቱ በኢትዮጵያ ለቲቢ መከላከል፣ ልየታ እና ሕክምና እያበረከተ የሚገኘውን አስተዋጽኦ በማድነቅ ድጋፉ በአጠቃላይ የጤናውን ዘርፍ ሥርዓት ለማጠንከር እንደሚረዳ መናገራቸውን የሚኒስቴሩመረጃ አመላክቷል፡፡
በቀጣይም ጤና ሚኒስቴር በበሽታ መከላከል፣ ለጤና ተቋማት የሕክምና መሳሪያ ሟሟላት እና መድሃኒቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከድርጅቱ ጋር በትብብር መሥራት እንደሚፈልግ ገልጸዋል፡፡