አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዲጂታል የተደገፈ የደረሰኝ ሥርዓት መዘርጋት የታክስ ገቢን ከማሳደግ አኳያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው ሲሉ የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴ ገለጹ፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር የታክስ አስተዳደር ስርዓትን ለማዘመንና ዲጂታላይዝ ለማድረግ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ የገቢዎችና የጉምሩክ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ሲካሄድ የቆየው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ተጠናቅቋል፡፡
በኮንፈረንሱ የተሳተፉት የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴ እንዳሉት÷ እያደገ የመጣውን የዲጂታል ኢኮኖሚ መሸከም የሚችል የታክስ አስተዳደር መገንባት አስፈላጊ ነው፡፡
በተለይም በዲጂታል የተደገፈ የደረሰኝ ስርዓት መዘርጋት የታክስ ገቢን ከማሳደግ አኳያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ነው ያስገነዘቡት፡፡
በአሁኑ ወቅት የትኛውንም የንግድ እንቅስቃሴ የትኛውም ቦታ ሆኖ መስራት እንደሚቻል ጠቁመው÷ የመረጃ ልውውጡን በቴክኖሎጂ አማራጭ ለመደገፍ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡
የኡጋንዳ፣ ኬንያ እና ሩዋንዳ ተሳታፊዎች የየሀገራቸውን የኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ፣ ኢ-ፋይሊንግ እና ኤክሳይዝ ታክስ አተገባበር በተመለከተ ተሞክሯቸውን አካፍለዋል፡፡
ገቢን ለማሳደግ የታክስ ህግ-ተገዥነትን ማስፈን እና የታክስ ሥርዓት አስተዳደርን ማዘመን እንደሚገባ መጠቆማቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡