Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ካንሰር አስከፊ ደረጃ ላይ ሳይደርስ በጊዜ ለማወቅ ምን ማድረግ ይገባል?

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ጤናማ ዘዴዎችን በመከተል በተለመዱ የካንሰር ህመም ዓይነቶች የመያዝ እድልን መቀነስ እንደሚቻል የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ካንሰር የአንዳንድ የሰውነት ህዋሶች ከቁጥጥር ውጭ መሆንና ተገቢ ባልሆነ መንገድ በማደግ ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ሲሰራጭ የሚከሰት ህመም ነው።

ከ100 በላይ የካንሰር ዓይነቶች የሰውን ልጅ ያጠቃሉ ተብሎ የሚታመን ሲሆን ፥ በአብዛኛው ምልክቶቻቸው ተብሎ የሚጠቀሰው እብጠት ፣ ያልተለመደ ደም መፍሰስ ፣ ረጅም ጊዜ የሚቆይ ሳል ፣ ምክንያቱ ያልታወቀ ክብደት መቀነስ እና ሌሎችም ናቸው፡፡

ዊኪፒዲያ ባወጣው መረጃ ደግሞ 22 በመቶው በካንሰር ምክንያት የሚከሰቱ ህልፈቶች(ሞቶች) በሲጋራ ማጨስ የሚመጣ ሲሆን ÷10 በመቶው ደግሞ ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ ደካማ አመጋገብና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ባለመስራት የሚከሰት ነው ብሏል፡፡

የካንሰር ተጋላጭነትን ለመቀነስና አስከፊ ደረጃ ላይ ሳይደርስ በጊዜ ለማወቅ ምን ማድረግ ይገባል?

በመጀመሪያ የተጠቀሰው መደበኛ የጤና ምርመራ ማድረግ ሲሆን ፥ የጡት፣ የማህጸን እና የአንጀት ካንሰርን አስቀድሞ በመለየት ካንሰሩ አስከፊ ሁኔታ ላይ ሳይደርስ ህክምና ለማድረግ እንደሚያስችል የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

ባለሙያዎች ከፍተኛ ተጋላጭነት ላላቸው ሰዎች የሳንባ ካንሰር ምርመራ እንዲያደርጉም ይመከራሉ ፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ክትባት ነው፡- ክትባት የካንሰር ህመም ተጋላጭነትን ለመቀነስ እንደሚረዳ የሚገለጽ ሲሆን ፥ እንደአብነት የሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ (ኤች ፒ ቪ) ክትባት አብዛኛዎቹን የማህጸን ካንሰሮችን እና ሌሎች በርካታ የካንሰር ዓይነቶችን እንደሚከላከል ይነገራል፡፡

በተጨማሪም የሄፐታይተስ ቢ ክትባት የጉበት ካንሰር ተጋላጭነትን እንደሚቀንስ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን መከተል ደግሞ ሌላው የካንሰር ተጋላጭነትን የሚቀንስ ነው ሲል ይገልጻል የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል(ሲዲሲ)፡፡

ጤናማ የሆነ ክብደት እንዲኖርዎ በማድረግ፣ ትንባሆ ወይም ሲጋራ ባለማጨስ፣ የሚጠጡትን የአልኮል መጠን በመገደብ እና ቆዳዎን ከፀሃይ በመጠበቅ፣ ዘወትር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን መከተል ይቻላል፡፡

በዚህም ለካንሰር የመጋለጥ እድልን መቀነስ ይችላሉም ብሏል ማዕከሉ።

Exit mobile version