አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ዘመቻ በክልል ደረጃ ተጀምሯል፡፡
የክትባት ዘመቻው ዛሬ በመቀሌ ከተማ ሐውቲ ክፍለ ከተማ የተጀመረ ሲሆን÷በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የመንግስት የሥራ ሀላፊዎችን ጨምሮ መንግስታዊ ያልሆኑና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ አካላት ተገኝተዋል፡፡
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የማህበራዊ ልማት ሴክሬታሪያት ካቢኔ ሀላፊ ክንደያ ገ/ህይወት (ፕ/ር)÷የክትባት ዘመቻው እንዲሰራ ሁሉም አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶክተር አማኑኤል ሀይለ በበኩላቸው÷በክልል ደረጃ ለ2 ሚሊየን ሕጻናት ክትባት ለመስጠት እቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡
ለእቅዱ መሳካት ቢሯቸው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እየሰራ መሆኑን መናገራቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በክልል ደረጃ የሚሰጠው የክትባት ዘመቻ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚሰጥ የተገለጸ ሲሆን÷ከ10 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ክትባቱን እንደሚወስዱም ተጠቁሟል፡፡