አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኩላሊት ህመም እንዳይስፋፋ ቅድመ መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
የኢትዮጵያ ኩላሊት ህመም ማህበር ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ጋር በመተባበር የኩላሊት አመታዊ ኮንፈረንስ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማን ጨምሮ የማህበሩ ከፍተኛ አመራሮችና አባላት በተገኙበት ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ኩላሊት ህመም ማህበርን ጨምሮ ማህበራት መንግስት ብቻውን መድረስ የማይችልባቸውን የጤና ጉዳዮች ላይ በመሳተፍና በመደገፍ ለህብረተሰቡ አገልግሎት በመስጠት ሚናቸውን እየተወጡ ነው።
መንግስትም ማህበራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በማገዝ ህብረተሰብ ተኮር ስራዎች ላይ በቅንጅት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በአሁን ወቅት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህ ረገድ ከሚመለከታቸው አጋሮች ጋር በትብብር እየተሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
የኩላሊት ህመም እንዳይስፋፋ በቅድመ መከላከል ላይ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ኩላሊት ህመም ማህበር ቅድመ መከላከል ላይ በመስራት በሽታው እንዳይስፋፋ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ልሳነ ሰይፉ በበኩላቸው፤ ህመሙን ለመከላከል በቅንጅት እንደሚሰራ አንስተዋል፡፡
ማህበሩ የተለያዩ ህብረተሰብ ተኮር ስራዎችን እንደሚሰራና የተለያዩ ሀገር አቀፍ ፖሊሲዎች ላይ ተሳትፎ እንደሚያደርግ ተናግረው፤ የተለያዩ ስልጠናዎችን ለባለሙያዎች በመስጠት፣ የኩላሊት ክብካቤ እና ግንዛቤ እንዲያድግ በማህበሩ በኩል መሰራቱን ገልጸዋል።
ማህበሩ የህክምና ባለሙያዎች፣ የኩላሊት ስፔሻሊስቶች፣ ነርሶች እና ግለሰቦችን በአባልነት የያዘ ነው።
በዘቢብ ተክላይ