Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በጂዳና አካባቢዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከጉዞ ሰነድና ፓስፖርት ጋር በተያያዘ ያለባቸውን ችግር ለመቅረፍ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጂዳና አካባቢዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከጉዞ ሰነድና ፓስፖርት ጋር በተያያዘ ያለባቸውን ችግር ለመቅረፍ ከአካባቢው ኮሚዩኒቲ አመራሮች ጋር ውይይት ተካሄደ፡፡

በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት የተመራ ልዑክ ከተለያዩ ግዛቶች ከተውጣጡ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ አመራሮች ጋር ተወያይቷል።

በጂዳ የኢፌዴሪ ቆንስል ከሚሸፍናቸው ሰባት ግዛቶች የተውጣጡ የኢትዮጵያ ዜጎች ተወካዮች በተሳተፉበት የውይይት መድረክ ዜጎች ከፓስፖርትና ህጋዊ ሰነዶች ጋር በተያያዘ እያጋጠማቸው ያለውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል ምክክር ተደርጓል፡፡

በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በወቅቱ እንዳሉት፤ የፓስፖርት እድሳት ችግርን ለመቅረፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል።

በዚህም ከዚህ ቀደም ህጋዊ ሰነድ ኖሯቸው ላመለከቱ ዜጎች የእድሳት አገልግሎት መሰጠቱን ተናግረዋል።

በቀጣይ የዜግነት ማጣራት ስራ በተለየ ትኩረትና ጥንቃቄ እንደሚሰራ ጠቅሰው÷ ለዚህም ኮሙዩኒቲው ህገወጥ ደላሎችን በማጋለጥ፣ ዜጎች በህጋዊ መንገድ ብቻ እንዲስተናገዱ ህብረተሰቡን በማንቃት ረገድ ከተቋሙ ጋር በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ከጉዞ ሰነድ ጋር በተያያዘ ያለውን ችግርን ለመቅረፍ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ቢመጣም ካለው ፍላጎት ጋር የተጣጣመ ባለመሆኑ አቅርቦቱን የማሻሻል ስራ እንደሚሰራ ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

Exit mobile version