አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ኖርዌይ ያላቸውን ዘርፍ ብዙ የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር ስቴን ክሪስተንሰን ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም በልማት ትብብር፣ በዘላቂ ሰላም ግንባታ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እና ለመቋቋም በሚከናወኑ ሥራዎች፣ በውሃ ሀብት አስተዳደር እና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች አጠቃቀም ዙሪያ የሁለቱን ሀገራት ትብብር ለማጠናከር የሚያስችል ምክክር አድርገዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ በዚህ ወቅት፤ ኖርዌይ የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ አጋር መሆኗን ገልጸው÷ ይህን ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ መንቀሳቀስ ይገባል ብለዋል።
በውሃ ሀብት አጠቃቀም እና በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ዙሪያ የሀገራቱን ግንኙነት አጠናክሮ ለመቀጠል መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
አምባሳደር ስቴን ክሪስተንሰን በበኩላቸው÷ ኖርዌይ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ ገልፀዋል፡፡
ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በሁሉም ዘርፎች አጠናክራ ትቀጥላለች ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።