አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተማ መሬት አያያዝን አስመልክቶ በኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በተዘጋጀ ጥናት ላይ ውይይት ተደረገ።
“የከተማ መሬት የሊዝ ገበያ ባህሪያት በኢትዮጵያ” በሚል በተካሄደው ውይይት ላይ የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) እንዳሉት፤ የከተሞች የመሬት አያያዝና አጠቃቀም ሊሻሻል ይገባል።
የመሬት አያያዝና አጠቃቀም ስርዓት ለከተሞች እድገትና ተጠቃሚነት ወሳኝ መሆናቸውንም አስገንዝበዋል።
በሀገሪቱ የሚገኙ ከተሞች ከደረሱበት የእድገት ደረጃና የማደግ ፍላጎት አኳያ የመሬት አያያዝና አጠቃቀም ክፍተት ያለበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ሊሻሻል እንደሚገባው አመልክተዋል።
በኢንስቲትዩቱ በ10 የክልል ዋና ከተሞችና ከተማ መስተዳደሮች ያደረገው የመሬት አያያዝ ጥናት የከተማ የመሬት ሊዝ ስርዓትን በተደራጀና በተቀናጀ የመሬት መረጃ አያያዝ ስርዓትን ማሻሻልና ቀጣይነቱ ላይ መስራት እንደሚገባ ጠቁሟል።
በሊዝ የተላለፉ መሬቶች ለታለመላቸው የልማት ስራ ላይ መዋላቸውን የሚከታተል ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባም በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡
በተጨማሪም በረጅም ጊዜ የመሬት ሊዝ አቅርቦትን ማሳደግ በፖሊሲ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት በስርዓት ሊመራ እንደሚገባና የከተሞችን ማስተር ፕላን ከግምት ውስጥ በማስገባት የመሬት አቅርቦቱን በተደራጀ መንገድ መፍትሄ ወደሚሰጥ አሰራር መግባት እንዳለበት አመላክቷል።
ጥናቱ የተገኙ ግኝቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ያመላከተ ሲሆን፤ በ10 ከተሞች 636 አልሚዎች ከወሰዱት መሬት ውስጥ 71 በመቶው ያልለማ መሆኑን ጥናቱ ጠቁሟል።
በሃይማኖት ኢያሱ