አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል በግብርናው ዘርፍ ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
አቶ ሽመልስ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው÷”የግብርናውን ዘርፍ ሙሉ በሙሉ ለማሻገር ካስቀመጥነው ግብ አንፃር ዘላቂነት፣ ብዛት፣ ፍጥነትና ጥራት የመሳሰሉ ጉዳዮች ወሳኝ ናቸው” ብለዋል፡፡
ይሄም የለውጥ ፖሊሲ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መታጠቅና ሳይንሳዊ ምርምሮች ላይ መመስረትን ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡
በዚህም ከኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትና በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር እየተሰራ እንደሚገኝ በመግለጽ ኢንስቲትዩቱም የምርምር ማዕከላትን አቋቁሞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ባለፉት ዓመታት አዳዲስ ዝርያዎችን እያሰራጨ የቆየ ቢሆንም የዚህ ዓመቱ ግን በብዛትም ሆነ በምርት ጥራት ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በዓመቱ 34 አዳዲስ የምግብ ሰብሎች፣ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች እና የከብት መኖ ዘር ቴክኖሎጂዎች ተለቅቀዋል ብለዋል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ 27ቱ የምግብ እህሎችና ሰባቱ የእንስሳት መኖ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ከተለቀቁት ዝርያዎች ስንዴ፣ ገብስ፣ ሩዝ፣ ዳጉሳ፣ ሞሴ፣ ስኳር ድንች እንደሚገኙበት አንስተዋል፡፡
ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ከመጨመር እና በአገር ውስጥ ከመተካት አንፃር ቡና፣ ስንዴ፣ የቢራ ገብስ፣ ሽምብራ፣ የቦሎቄ ዝርያዎች እንዲሁም ድምብላል ይገኛሉ ብለዋል፡፡
አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በምርት ውስጥ ካሉ የተሻሻሉ ዝርያዎች የ10 በመቶ ምርታማነት ብልጫ እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡
ለፋብሪካዎችና ለውጭ ገበያ የሚያስፈልጉት የጥራት ደረጃዎችን የሚያሟሉ ናቸው ያሉት አቶ ሽመልስ÷የዝናብ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች በፍጥነት የሚደርሱ ዝርያዎችን እንዲሁም በቂ ዝናብ ባለባቸው አካባቢዎች እርጥበት መቋቋም የሚችሉ ዝርያዎች እንደተሰራጩ አስታውሰዋል፡፡
በዚህ ዓመት ከብዙ ልፋት በኋላ ከማቻራ እና ከሲናና ግብርና ምርምር ማዕከላት ጋር በመተባበር ሁለት ከፍተኛ ምርት የሚሠጡ አዳዲስ የቡና ዝርያዎችም ተለቅቀዋል ብለዋል፡፡
ዘንድሮ በተሰራጩ ዝርያዎች ሥራ ላይ ስድስት የግብርና ምርምር ማዕከላት የተሳተፉ ሲሆን÷የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በክልልና በሀገር ደረጃ ቀዳሚ ስፍራ ይይዛል ነው ያሉት፡፡
የኦሮሚያ ክልል በግብርናው ዘርፍ ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው÷በቀጣይም የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ከባለድርሻ አካላት ጋር መስራቱን ይቀጥላል ብለዋል፡፡